"የኛ ለሁሉም!"

ስለ የኛ

“የኛ ለሁሉም!”

የማይክሮ ፋይናንስ ኢንዳስትሪ በዓለማችን ላይ ከሶስት አስርት ዓመታት ታሪክ ያልበለጠ ቢኖረውም እጅግ በጣም በአስደናቂ ሁኔታ በመስፋፋትና በፍጥነት ዕድገት በማስመዝገብ አሁን ላይ ዋነኛና አስፈላጊ የዓለም አጀንዳ ሆኗል፡፡ የአነስተኛ ፋይናንስ ኢንዳስትሪ ዋነኛ ደንበኞች አብላጫ ቁጥር ያላቸው በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙት መስራት የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

የማይክሮ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው ዓላማ የኢንዱስትሪውን ትርፋማነትና ዘላቂነትን በማስጠበቅ በንግድና በተለያዩ የስራ መስክ ላይ መሰማራትና ሀብት መፍጠር የሚችሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ደንበኞች ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡

በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ በዝቅተኛ እና መካከለኛ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ የሚመደቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መስራት የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የፋይናንስ አገልግሎት አልተሟላላቸውም፡፡ በተለይም በኢኮኖሚው ንቁ የሆነ ተሳትፎ ያላቸውና በመላው ሀገሪቱ ውስጥ በጥቃቅን ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እሴት የሚጨምሩ ፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ገቢ የሚያስገኙትን ኢላማ ያደርጋል፡፡

የኛ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ የተመሰረተው የላቀ የሞያ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ አገልግሎት ለሚፈልጉ ግለሰቦችና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራየዝ ለታቀፉ ህጋዊ ማህበሮች በመስጠት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ሀብት ለመፍጠርና ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡

የኛ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማትን ለማቋቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 626/2001 እንዲሁም በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1164/2012 መሠረት ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ንግድና ኢንዳስትሪ ሚኒስተር በንግድ ምዝገባና የፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሠረት ህጋዊ ፍቃድና ምዝገባ በማግኘት በህጋዊነት አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ባለአክሲዮኖች ዓላማቸውን በተሟላ ሁኔታ ማሳካት የሚችሉ ፣ በብርቱ ጥረታቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚያመጡ ፣ ወጣቶች ፣ የተማሩ ፣ በቂ ልምድ ያላቸው ፣ ቁርጠኛ እና ሥራ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡

የኛ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ በብርቱ መስራች አባላት በ40 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ነው፡፡ ኩባንያችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ ዋና ዋናዎቹም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፣ የኢትዮጵያ የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ማህበር ፣ የመንግሥትና የግል ንግድ ባንኮች ፣ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ፣ ማርኮን የመኪና አስመጪ፡፡